የኩፍኝ በሽታ

የኩፍኝ በሽታ በጣም ተላላፊ የሆነ በሽታ ነው። በተለይም ለትንንሽ ልጆች፣ ከባድ እና እንዲያውም ገዳይ ሊሆን ይችላል። የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል ደህንነቱ የተጠበቀ እና በጣም ውጤታማ የሆነ ክትባት አለ። የኩፍኝ ክትባት እድሜው 1 አመት እና ከዚያ በላይ ለሆነ እያንዳንዱ ሰው ይመከራል። በዋሽንግተን ግዛት በትምህርት ቤት እና የልጅ እንክብካቤ ማዕከል ለመሳተፍ የኩፍኝ በሽታ ክትባት ያስፈልጋል። እንዲሁም በልጅ እንክብካቤ ማዕከል ወይም ቅድመ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች ያስፈልጋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ፣ “Measles, Mumps and Rubella (MMR፣ ኩፍኝ፣ ጆሮ ደግፍ እና የጀርመን ኩፍኝ)” እና “Measles, Mumps, Rubella and Varicella (MMRV፣ ኩፍኝ፣ ጆሮ ደግፍ፣ የጀርመን ኩፍኝ እና ቫሪሴላ)” የሚባሉ የኩፍኝ በሽታ ክትባቶች ይገኛሉ።

የኩፍኝ በሽታ ቫይረስ መረጃ

  • የኩፍኝ ቫይረስ በአየር ውስጥ ይጓዛል። ቫይረሱ የኩፍኝ በሽታ ያለበት ሰው በነበረበት ክፍል አየር ውስጥ እስከ ሁለት ሰአታት ድረስ ስለሚቆይ ቫይረሱ ያለበት ሰው አቅራቢያ ከሄዱ ኩፍኝ ሊይዝዎት ይችላል።
  • በሽፍታ ከመያዛቸው ቀደም ብሎ ከ4 ቀናት በፊት እና ሽፍታው ከታየ በኋላ እስከ 4 ቀናት ድረስ በበሽታው ከተያዘ ሰው የኩፍኝ በሽታ ሊይዝዎት ይችላል።
  • በሽታ የመከላከል አቅም የሌለው እያንዳንዱ ሰው ለኩፍኝ ቫይረስ ከተጋለጠ በኩፍኝ በሽታ ይያዛል።
  • የውጪ ሃገር ጉዞ ወይም ለውጪ ሃገር ተጓዦች መጋለጥ የኩፍኝ በሽታ ተጋላጭነትን ይጨምራል።

የኩፍኝ በሽታ፣ እንዲሁም የጀርመን ኩፍኝ የሚባለው፣ ከሁሉም የልጅነት የሽፍታ/ትኩሳት በሽታዎች በይበልጥ ገዳይ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ የልጆች ሞት ቀዳሚ መንስኤ ነው። የ U.S. Centers for Disease Control and Prevention (የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል) ስለ አገር አቀፍ የኩፍኝ በሽታ ወረርሺኝ (በእንግሊዘኛ እና በስፓኒሽ ብቻ) መረጃ አለው።

የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል የተሻለው መከላከያ ክትባት መውሰድ ነው። የኩፍኝ ክትባቱ ደህንነቱ የተጠበቀ እና በጣም ውጤታማ ነው። እራስዎን እና ልጆችዎን በኩፍኝ፣ ጆሮ ደግፍ፣ እና የጀርመን ኩፍኝ (MMR) ክትባት (ሊንኩ በእንግሊዘኛ እና በስፓኒሽ ብቻ) መከላከልዎን ያረጋግጡ።

የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች 

An infant with measles

የኩፍኝ በሽታ የሚጀምረው በ፦

  • ትኩሳት
  • ተቅማጥ
  • ሳል
  • የአፍንጫ ፈሳሽ
  • ቀይ እና በእንባ የተሞሉ ዓይኖች
  • የድካም ስሜት

ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ሽፍታ ይጀምራል፣ ይህም አብዛኛውን ጊዜ ፊት ላይ ጀምሮ በሙሉ ሰውነት ላይ ሊሰራጭ ይችላል።

በአንዳንድ ሰዎች፣ በተለይም ስር የሰደደ የህክምና ችግር ያለባቸው፣ ነብሰጡር የሆኑ፣ ወይም የተመጣጠነ ምግብ እጦት ባለባቸው ሰዎች ላይ፣ የኩፍኝ በሽታ እንደ የሳምባ ምች፣ የአንጎል ጉዳት፣ ዓይነ ስውርነት፣ መስማት መሳን፣ እና ሞት የመሳሰሉ ከባድ ችግሮችን ያስከትላል።

የኩፍኝ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ከ 7 እስከ 10 ቀናት ይቆያል።

ስለ MMR ክትባት

MMR ክትባት (ሊንኩ በእንግሊዘኛ እና በስፓኒሽ ብቻ) ከኩፍኝ፣ ከጆሮ ደግፍ፣ እና ከጀርመን ኩፍኝ ይከላከላል። MMRV የሚባለው፣ ሌላኛው ክትባት፣ ከእነዚያ ሶስት በሽታዎች እና ከጉድፍ ይከላከላል። በዩናይት ስቴትስ ውስጥ የኩፍኝ-ብቻ ክትባት የለም።

ልጆች ሁለት ዶዝ መውሰድ አለባቸው፦ አንድ ዶዝ በ12 እና በ15 ወራት መካከል፣ እና ሁለተኛው በ4 እና በ6 አመት መከላከል። ቤተሰብዎ ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ የሚጓዝ ከሆነ፣ ልጅዎ ከ6 እስከ 12 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ዶዝ መውሰድ ይችላል።

ከ1956 በኋላ የተወለዱ አዋቂዎች አስቀድመው ካልወሰዱ የMMR ዶዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

ለልጆችዎ የ MMR ወይም MMRV ክትባት ለማግኘት የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎን ያነጋግሩ። ዋሽንግተን MMR እና MMRV ክትባቶችን እስከ 18 አመት ላሉ ህጻናት ያለ ምንም ወጪ ያቀርባል፣ እና በግዛቱ ካሉ የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎች ያገኟቸዋል። አቅራቢዎች ለቢሮ ጉብኝት ክፍያ እና ክትባቱን ለመስጠት፣ መድሃኒት መስጫ ክፍያ ተብሎ የሚጠራ ክፍያ ሊያስከፍሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ፣ የመድሃኒት መስጫ ክፍያ መክፈል ካልቻሉ፣ አቅራቢዎ እንዲተውሎት ሊጠይቁ ይችላሉ።

እርስዎ ወይም ልጅዎ ከዚህ በፊት MMR፣ MMRV፣ ወይም ሌላ የኩፍኝ በሽታ ክትባት ከወሰዱ ነገር ግን ክትባቱን የሚያሳይ የህክምና መዝገብ ከሌለዎት፣ እርስዎ ወይም ልጅዎ የ MMR ወይም MMRV ዶዝ መድገም ሊኖርብዎት ይችላል። ከዚህ በፊት ለወሰዱት ሰዎችም ቢሆን፣ ተጨማሪ የክትባት ዶዞችን መውሰድ ምንም ችግር የለውም።

በዋሽንግተን ግዛት፣ በልጅ እንክብካቤ፣ በ Early Childhood Education and Assistance Program (ECEAP፣ የመጀመሪያው የልጅነት ጊዜ ትምህርት እና የድጋፍ ፕሮግራም)፣ እና በ Head Start (ሄድ ስታርት) ተቋማት ውስጥ ያሉ ሰራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል መከተብ አለባቸው።

ሌላ የኩፍኝ ክትባት ዶዝ የማይፈልጉ ከሆነ፣ የበሽታ የመከላከል አቅም እንዳለዎት ለማወቅ ሃኪምዎ ምርመራ እንዲያደርግልዎት መጠየቅ ይችላሉ። ይህ የጸረ እንግዳ አካል መጠን ይባላል። የመድህን ዋስትና ይህንን ምርመራ ላይሸፍን ይችላል።

ሁላችንን ለመጠበቅ በጋራ እንቁም፦ የ Jaxon ታሪክ

በዋሽንግተን፣ ፖርት ኦርቻርድ፣ የምትኖረው Paula Abalahin የልጇን የ Jaxon ን ታሪክ አጋርታለች፦

Paula hugging Jaxon

 
ልጄ Jaxon የ 7 ወር ልጅ እያለ በኩፍኝ ተያዘ፣ ክትባት ለመውሰድ በጣም ትንሽ ነበር። ተሻለው፣ ነገር ግን ከአምስት አመት በኋላ በሚጥል በሽታ መታመም ጀመረ። የመዋጥ፣ የመናገር፣ እና የመራመድ አቅም አጣ። በጣም ከተሰቃየ በኋላ፣ ጃክሰን ከጥቂት አመታት በኋላ ሞተ። ህመሙ የተከሰተው በኩፍኝ ቫይረስ ነው።

“ምንም እንኳን ውጤታማ ክትባት ቢኖርም፣ የኩፍኝ በሽታ አሁንም በአለም አቀፍ ደረጃ የታዳጊ ህጻናት ሞት ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ አውቀናል። እናም በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ሙሉ በሙሉ አያስከትቡም፣ ይህም በኩፍኝ በሽታ እና በሌሎች አስከፊ በሽታዎች ለመያዝ እና ለማሰራጨት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ታሪኬ ሌላ ልጅ ልጄ ያለፈበት ነገር እንዳይደርስበት ለመከላከል ሊረዳው እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።”

የኩፍኝ በሽታ መርጃዎች

የኩፍኝ በሽታ መርጃዎች በእንግሊዘኛ ብቻ